ስለ ማህበራችን አጭር መግለጫ

ወሎ የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማህበር

«ወሎየነት መለያችን፣ኢትዮጵያዊነት ማንነታችን»

 

ወሎ ስንል፦

“ወሎ” ሰፊና ጠባብ ትርጓሜ ሊሰጠው ይችላል። ሆኖም ግን ይህንኑ አሻሚ ትርጉም ለማቃለል በወል አጠራር “ወሎ” ስንል በዘውዳዊው ሥርዓት ዘመን እንደነበረው 12 አውራጃዎችን ያካተተውን ክፍለ-ሃገር ማለታችን ነው።

· ወሎ ብዙ የፖለቲካ ሃይላት ለስልጣንና እንዱ አንዱን ለማስገበር የተፋለሙባት፣ ለአያሌ ዘመናት በአብሮነት የታሪክ ቁርኝት ጉዞዋ ሕዝቦቿ በደምና በእርቅ፣ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሃይማኖታዊ መስተጋብር እንደ ውሃና ወተት፣ እንደ ሳርና ጭድ ድርና ማግ ሆነው የተወሳሰቡባትና የተዋሃዱባት ምድር ናት።

·         ወሎ በአገው የዘር ግንድና በሌሎች ሕዝቦች ቅርንጫፍነት ያበበች አውራ “የቤተ - ዐማራ” ዛፍ ስለመሆኗ ብዙ ማስረጃዎች አሉ።

 

ባህሎቿ፦

በሕዝቦቿ ስብጥርና በአቀማመጧ የታሪካዊ ኢትዮጵያ ባህልና እምነት እምብርት ስለመሆኗ ብንጠቅስ፦

·         ጥንታዊ የአርሶ-አደርና የእርባታ ግብርናዎች፣

·         የረቀቁ የምግብ፣ የልብስ፣ የስጋጃና የሸክላ ሥራ ሙያዎች፣

·         የአራቱ ቅርሳዊ የሙዚቃ ስልቶች (አንቺሆየ፡አምባሰል፡ባቲና ትዝታ)፣

·         ከየትኛውም ክፍለ ሃገር ብዛትና የራሳቸው ልዩ መገለጫ ያላቸው ባህላዊ የሙዚቃ አጨዋወትና ድልቂያዎች (የሰቆጣ፣ የራያ፣ የቃሉ፣ የቦረና-ሳይንት እና የደሴ ዙሩሪያ ወ.ዘ.ተ.)፣

·         ሃይማኖት-ነክ ዝማሬዎች (የኦሮቶዶክስ ክርስቲያን)፡ ውዳሴዎች (የሱፊ ሙስሊም መንዙማዎች)፤

·        የግዕዝ ስነ-ጽሁፍና ሌሎች ነባር ውርሶችዋና ቅርሶችዋ ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ታሪካዊ ማንነት ህያው ማሳያ ዋቢዎች ናቸው፣

 

ታሪኳ፦

በፖለቲካ ታረክም ወሎ ቁልፍ ሚና ተጫውታለች፦

·         የአገው ዛጉየ ስርዎ-መንስት አክሱም ስትፈርስ እሴቶቿን ተቀብሎ ክርስትናን ወደ ወሎ በጌምድርና ስሜን፣ እንዲሁም ጎጃምና ሸዋ ያስፋፋ፣

·         ላሊበላን የሚያክል የአለም ቅርስ ያወረሰ፣

·         ኃይቅ እስቲፋኖስ ደግሞ መሪነቱን በተራዋ ተቀብላ የስሜኑን ስልጣኔ ወደ ጎጃም፡ ሸዋና እናርያ ያስፋፋች የኦርቶዶክስ ክርስትና የሰበካና የጽሑፍ ማዕእከል፣

·         ወረሂመኖና አርጎባም ለመላ ኢትዮጵያ የእስልምና ትምህርት ማዕከሎች፣

·         ከጎንደር እስከ ሸዋ ማእከላዊ መንግስታት ድረስ ብዙ ነገስታትን፣መሳፍንትና አርበኞችን ያፈራች ታላቅ ራስ-ገዝ ክፍለ-ሃገራት (ላስታ፣የጁ፣ መሃል-ወሎ) የነበሩባት መሬት ናት።

 

የዛሬ ሕዝቧ

ዛሬ በመልክና በገጽታ ወሎ ዉስጥ የምናየው ሁሉ የነዚህ የታሪክ ሂደቶች የፍልሰት ውጤቶች ናቸው። የዛሬይት ውሎ ሕዝብ፦

·         98% በአማርኛ አፉን የፈታና ከ95% በላይ ደግሞ በአማራ ማንነት ራሱን ያስመዘገበ፣

·         ወደ 9 ሚሊዮን የሚገመትና በመላ እትዮጵያና በሁሉም አህጉሮች የሚገኝ፣

·         ግማሽ ሙስሊምና ግማሽ ክርስቲያን የሚገመት፣

·         የአማራ፣ የአፋር፣የኦሮሞ፣የትግሬ፣የአርጎባና፣የአገው ነግዶችን የሚያካትት፣

·         ጎሳ፣ ሃይማኖት፣ ቆለኛና ደገኛ ሳይባባል በመቻቻል፣ በመከባበር፣ በመፈቃቀድና በመረዳዳት አብሮነት አክብሮና ጠብቆ በማቆየት ለዓለም መልካም ዓርዐያ እስከመሆን የደረሰና፣

·         በትውልድ ቦታው የሚኮራ፣ ታታሪ፣ በአስተዳደሮች ቢበደልም ኢዮጵያዊነቱን ጥያቄ ያላስገባ ታማኝ አርበኛ ዜጋ መሆኑ የመቅደላና የአድዋ ምስክርነቶችን መጥቀሱ ብቻ በቂ ነው።

===================================================

ይህ የሲቭል ስብስብ ለምን

ከዚህ በፊት በወሎ ልማት ማህበራት ብዙ ተመክሮና ተሞክሮ እንዳለ እንገነዘባለን፦

·         አሁን ያነሰሳን ጥሪ “በሁለ-ገብ ህዝባችንና አገራችንን እናድን” የሚለው የክተት ጥሪ ነው።

·         ወሎን እንደምርኩዝ አድርገን ያቋቋምነው ማህበር ከጎጠኝነትና ከዘረኝነት የራቀ ነው።

·         “ወሎየነት መለያችን፤ኢትዮጵያዊነት ማንነታችን” የሚለው መሪ ቃላችን ሠፊ ምህዳር ያቀፈ ሰላማዊና ሕጋዊ አለም-አቀፍ ንቅናቄ ነው።

የውርስና ቅርስ ተልዕኮዎች

ኢትዮጵያዊ ወሎ ውርስና ቅርስ ማህበር አምስት አንኳር እሴቶች፣መርሆዎችንና ማንነቶችን ያካትታል፦

·         መለያችን ውሎየነት በባህሎቹ ባለጸጋ መሆኑ እንዲቀጥልና በዘመናዊነት እንዲዳብር መርሃግብር አዘጋጅቶ ለመስራት፣

·        በአማራነታቸው በሃገራቸው ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ እውጭ አገራት አድልዎ የሚደርስባቸው ወሎየዎችንና በአጠቃላይ ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን ለመታደግ፣

·         ሙሉ የዴሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ መሟገትና አጋር የመብት ታጋይ ድርጅቶችን ለመርዳት መዘጋጀት፣

·         ከሃይማኖት፣ከጎሳ፣ከጾታ፣ከመደብና ከክልል-ፖለቲካ ጠንቆች የጸዳች ኢትዮጵያን ለመገንባት ከሚታገሉ አጋር ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራትና፣

·         እነዚህን አላማዎችና ግቦች በስራ ለማዋል የሰው ሃይልና የገንዘብ ማሰባሰብ ናቸው።

 

*** ወሎ ታብባለች፥ ኢትዮጵያም ለዘላለም ትኖራለች ***